ረሀብ በዓለም ላይ እጅግ በጣም የገዘፈ ችግር ነው፡፡ ሆኖም ሊፈታ የሚችል ችግር ነው፡፡ የቬልትሁንገርሂልፌ (Welthungerhilfe) ራዕይ እያንዳንዱ ሰው ሰብአዊ ክብር ኖሮት፣ ከረሀብና ከድህነት ነፃ ሆኖ በራሱ የሚመራበትን ሕይወት የሚኖርበትን ማየት ነው፡፡
የቬልትሁንገርሂልፌ እስትራቴጃዊ ግብ በተባበሩት መንግስታት ሁለተኛው ዘላቂ ልማት ግብ ላይ ተመስርቶ እኛ በምንሠራባቸው አካባቢዎች ሁሉ እስከ 2030 (እኤአ) ረሀብን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ነው፡፡ እኛ በንቃት በምንቀሳቀስባቸው አገሮች ሁሉ ከአካባቢው ተባባሪ አካላት ጋር በመሥራት ረሀብን ለማጥፋት እንፈልጋለን፡፡ የሥራ እንቅስቃሴዎቻችን የዛሬና የወደፊት ትውልዶች ጤናማ አካባቢና የሚተሳሰብ ማህበረሰብ እንዲኖራቸው በመርዳት ዕጣ ፈንታቸውን ማሻሻልን ታሳቢ ያደረጉ ናቸው፡፡
ረሀብን የማጥፋት የአሠራር ዘዴ
በዓለምአቀፍ ደረጃ ረሀብን ለማጥፋትና ለዘለቄታዊ የምግብ ዋስትና እንታገላለን፡፡ ይህም ትግላችን ጤናን፣ ትምህርትንና የኢኮኖሚ ልማትን ከማሻሻል ጎን ለጎን በተወሰነ አካባቢ ላይ የሚከናወን ግብርናን፣ የንፁህ ውሃና ለተፈጥሮ አካባቢ የሚስማማ ንፁህ ኢነርጂ አቅርቦትን ያካትታል፡፡
ላን ፕላስ LANN+ ሥልጠና የሚለው መታወቂያችን የገጠር ቤተሰቦች የምግብና የተመጣጠነ ምግብ (የአልሚ ምግብ) ዋስትና እንዲቀዳጁ ማድረግ ነው፡፡ እኛ ጠቃሚ ውሳኔዎችን በማስተላለፍ ሂደት ውስጥ ሴቶች እንዲካተቱ ክፍተኛ ትኩረት እንሰጣለን፡፡
ከዚህ ጋር የሚካተተው በተወሰነ-አካባቢ ላይ ለሚከናወን እርሻ የምንሰጠው አትኩሮት ነው፡፡ በተወሰነ-አካባቢ ላይ የሚከናወን እርሻ ለተፈጥሮ አካባቢ እንክብካቤ እየተደረገ ረሀብንና ድህነትን ለመዋጋት እንዲቻል ብዙ ምርት የሚያስገኙና የበለጠ አልሚ ንጥረ ነገር ያላቸውን የእህል ዓይነቶች ባለአነስተኛ ይዞታ ገበሬዎች እንዲያመርቱ ማገዝ ነው፡፡
ቬልትሁንገርሂልፌ በገበያ ተኮር የአሠራር ዘዴዎች አማካይነት የማህበረሶችን አቅም ይገነባል፡፡ የአሠራር ዘዴዎቹ ሕዝቡ ከግብርና በሚያገኘው የምርት ውጤቶች ሕይወቱን መምራቱን እንዲቀጥልበት ማስቻል ነው፡፡ ከዚህም ሌላ የገጠር ቤተሰቦች ምግብ የማግኘት መብታቸው በዓለምአቀፍ ደረጃ በሚቀርቡ የግብርና ምርቶች ፍጆታና በንግድ ምክንያት እንዳይደናቀፍ ለማድረግ እንዲቻል የምግብ ዋስትና ደረጃ ፕሮጄክት ለመቅረጽ ድጋፍ እንሰጣለን፡፡
የቬልትሁንገርሂልፌ ፕሮጄክቶች በግጭትና በአየር ለውጥ ምክንያት በተጎዱ አገሮች ውስጥ የመቋቋም አቅማቸውን ያሳድጋል፡፡ ማህበረሰቦች ወደፊት ሊገጥማቸው ለሚችለው ቀውስ በተሻለ ደረጃ ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ለማድረግ የአጭር ጊዜ አስቸኳይ እርዳታ እንቅስቃሴዎች ከረጅም ጊዜ የልማት ፕሮግራሞች ጋር እንዲቀናጁ (እንዲተሳሰሩ) ተደርገዋል፡፡፡
ቬልትሁንገርሂልፌ በሰብአዊ መብት አስተምህሮ የአሠራር ዘዴ የሲቭል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በታችኛው እርከን ያጠናክራል፡፡ ይህን የሚያደርገውም ወደ ጎን የተገፉ ወገኖችን የመብት ባለቤቶች (ዕርዳታ ተቀባዮች ሳይሆኑ) አድርጎ በመቀበልና ምግብ ለማግኘት ጥያቄያቸውን በንቃት እንዲያቀርቡና መሬት ፣ ንጹህ ዉሃና ዘር ለማግኘት አጥብቀው እንዲጠይቁየሚያግዛቸውን መሣሪያ በመስጠት ነው፡፡
የፖለቲካ ሁኔታዎችን ለመለወጥ የሚንቀሳቀሱ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችንም (መያድ) እንደግፋለን፡፡ የምንደግፈውም በሲቭል ማህበረሰብ (ሶሳይቲ) ቡድኖች፣ በፖለቲካ ባለሥልጣናትና በባለሀብቶች (ኢንቨስተሮች) መካከል በእኩል ደረጃ ውይይት እንዲካሄድ በማበረታታት ነው፡፡
ራስን በራስ ለመምራት መጣጣር
ዓላማችን የሕዝቦችን ሕይወት በረጅም ጊዜ ሂደት ማሻሻል ነው፡፡ በመሆኑም‘ራሱን እንዲረዳ እርዳው’ በሚለው መርህ ላይ ተመስርተን እንሠራለን፡፡ ፕሮግራሞቻችን ሰዎች የራሳቸውን ሕይወት ራሳቸው እንዲመሩና ምግብ የማግኘት ሰብአዊ መብታቸውን ለማረጋገጥ እንዲችሉ ተደርገው የተቀረጹ ናቸው፡፡
የቬልትሁንገርሂልፌ የአሠራር ዘዴዎች በአንድ የተወሰነ የፕሮጄክት ሥራ እንቅስቃሴዎችና የፖለቲካ አስተምህሮ ሥራ ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡ ይልቁንም ሊመዘኑ የሚችሉ ውጤቶችና ለባለድርሻ አካላት፣ ለለጋሾችና በፕሮጄክቱ አካባቢ ለሚገኘው ሕዝብ ተጠያቂ መሆን ላይ የሚመሰረት ነው፡፡
በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የረሀብ ማብቂያውን አሁን እየደረስንበት ነው፡፡ እንደበርካታዎቹ በልማት ትብብር ሥራዎች ላይ የተተሳተፉ ብዙ ወገኖች ሁሉ ወደ ፊት በአንድ ወቅት ላይ ሥራችን አስፈላጊነቱ እንደሚያበቃ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ይህን ራዕያችንን እንድንቀዳጅ አግዙን፤ ከረሀብ ነፃ ለሆነች ዓለም በምናደርገው ትግል ተሳተፉ፡፡