ቬልትሁንገርሂልፈ የረሀብ መንስኤዎች ላይ በመስራት ረሀብ ለሌለበት ዓለም በቁርጠኝነት በመታገል ላይ ይገኛል፡፡ ከፖለቲካና ከሃይማኖት ነፃ ሆነን በመንቀሳቀስ በጀርመን ከሚገኙት ትላልቅ የግል የእርዳታ ድርጅቶች አንዱ ሆነናል፡፡
የሥራ እንቅስቃሴዎቻችን ‘ራሱን እንዲረዳ እርዳው’የሚለውን መርህ የሚከተሉ ናቸው፡፡ በተጨማሪም የተባበሩት መንግስታት የዘላቂ ልማት ግብ፡- ረሀብን በ2030 (እኤአ) ማጥፋት ከሚለው ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ከአካባቢው ተባባሪዎች ጋር በቅርበት ሠርተን ሊመዘን የሚችል በጎ ተጽዕኖ፣ ሀቀኝነትንና ተጠያቂነትን በማስፈን ማህበረሰቦች ከረሀብና ከድህነት ዑደት እንዲወጡ አቅማቸውን እናሳድጋለን፡፡
ቬልትሁንገርሂልፈ ከ1962 (እኤአ) ጀምሮ ከአገር ውስጥና ዓለምአቀፍ ተባባሪ ድርጅቶች ጋር በመሆን በ70 አገሮች የሥራ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ይህንኑ ሲያደርግ የቆየው ሕዝቦች የራሳቸውን ሕይወት በራሳቸው እንዲመሩና ምግብ ለማግኘት ያላቸውን መብት ለዘለቄታው እንዲያገኙ ለማስቻል ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከ67 አገሮች የተገኙ ከ2450 በላይ ሠራተኞች ከ400 በላይ ፕሮጄክቶችን በ37 አገሮች እተገበሩ ይገኛሉ፡፡
ቬልትሁንገርሂልፈ በልዩ ልዩ የረሀብ መንስዔዎች ላይ በመስራት የሕዝቦችን የተወሰኑ ፍላጎቶች ለማሟላት ሲባል አስቸኳይ እርዳታን፣ መልሶ ማቋቋምንና የረጅም ጊዜ የልማት ሥራዎችን ያቀናጃል፡፡
እኛ ለግልጽነትና ጥራት ላለው አመራር ከፍተኛ ቁርጠኝነት አለን፡፡ እንደ ሥነምግባር መመሪያ፣ የማኔጅሜንት ጥራት ሂደቶቻችንና ዓመታዊ ዘገባችን ያሉ የቬልት ሁንገር ሂልፈ እርምጃዎች አብረን የሥራ እንቅስቃሴ በምናካሂድባቸው ማህበረሰቦች ውስጥ የለጋሾች ገንዘብ ክፍተኛ በጎ ተጽዕኖ የሚፈጥር መሆኑን ያረጋግጣሉ፡፡
ድርጅታዊ መዋቅራችን
በአንድ ወቅት ሥልጣን ላይ የሚገኝ ማንኛውም የጀርመን ፕሬዚዳንት ቬልት ሁንገር ሂልፌ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ድጋፍ የሚሰጡ የተከበሩ የድርጅቱ ሰው ናቸው፡፡ ቬልትሁንገርሂልፌ ፕሬዚዳንቱና የአማካሪው ቦርድ ሌሎች አባላት ድርጅቱን በውጭ የሚወክሉና የሥራ አስፈጻሚ ቦርድን የሚያማክሩ ናቸው፡፡ ሙሉውን ጊዜውን በድርጅቱ ሥራ ላይ የሚያውለው የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ የቬልት ሁንገር ሂልፌን የሥራ እንቅስቃሴዎች ይመራል፡፡
ሊቀ መንበሩና ሌሎች የቦርድ አባላት በቬልት ሁንገር ሂልፌ ደንብና ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔዎች ላይ ተመርኩዘው ይሰራሉ፡፡ አባላቱ የፌደራል ፓርላማ ፕሬዚዳንት፣ የጀርመን ፓርላማ ቡድኖች መሪዎች፣ አብያተክርስቲያናት ፣ ሌሎች ቡድኖችን የሚጨምሩ ማህበራት የሚካተቱበት ነው፡፡
የባለአደራ ቦርድ የሕዝብ ግንኙነትንና የገበያ ጉዳዮችን በሚመለከት አማካሪ ቦርድንና የሥራ አስፈጻሚ ቦርድን ያማክራል፡፡ የፕሮግራም አማካሪ ኮሚቴ ደግሞ የፕሮግራም ፖሊሲዎችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ኃላፊነት አለበት፡፡